ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ 18ኛዉን ዓለም ኣቀፍ ሙስናን የመከላከል ቀን በማሰብ ዉይይት ኣካሄደ
በኣለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ በሓገራችን ለ17ኛ ጊዜ የተከበረዉን ሙስናን የመከላከል ቀን በማሰብ በዩኒቨርሲቲዉ የሥነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ኣዘጋጅነት “በሥነ-ምግባር የታነፀ ኣመራር ከሙስና ለፀዳች ኢቲዮጲያ“ በሚል መሪ ቃል ዉይይት ተካሄደ።
ዉይይቱን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሙክታር መሓመድ እንዳሳሰቡት እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲዉ ሰራተኛ በየዓመቱ ቀኑን በማሰብ ዉይይት ከማካሄድ ባለፈ በተሰማራበት የስራ መስክ የሚጠበቅበትን ሁሉ በመወጣት ለተሻለ ተቋማዊ ግንባታ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ ኣሳስበዋል።
ለዉይይቱ የመነሻ ሃሳብ የሚሆን ፅሑፍ ያቀረቡት የማህበራዊ እና ሰብዓዊ ኮሌጅ ዲን ኣቶ ፈይሳ ደበላ እንደገለፁት፡
የዲሞክራሲያዊ ባህሎች ያለመዳበር
ተጠያቂነት እና ግልፅነት ያለመኖር
ግልፅ እና ሙስናን የሚያወግዙ ህጎች ያለመኖር
ሙሰኞች ላይ ተገቢዉን ህጋዊ እርምጃ ለመዉሰድ ቁርጠኛ ያለመሆን
በኣህጉራችን ብሎም በሓገራችን መንግስታዊ ኣገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዉስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣዉ የሙስና ችግር ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸዉን ኣብራርተዋል። በመሆኑም እነዚህን ተቋማት ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ተላብሶ መምራት߹በተቋማቱ ዉስጥ ግልፀኝነት እና ተጠያቂነትን ማስፈን߹ በተቋማቱ ዲሞክራሲያዊ እሴቶች እና መርሆች እየዳበሩ እንዲሄዱ መስራት እና መልካም ኣስተዳደርን ማስፈን ወረርሽኑን ለመቋቋም ይረዳሉ ሲሉ ኣክለዋል፡፡
በመጨረሻም በቀረበዉ የመነሻ ሃሳብ ላይ ሰፊ ዉይይት ተካሄዶ እያንዳንዱ የዉይይቱ ተሰታፊ በተሰማራበት የስራ መስክ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማበርከት የሙስና ትግሉን ከራሱ ለመጀመር ቃል በመግባት ዉይይቱ ተቋጭቷል፡፡